የሽሮዲንገር ቱርክ
ረጀብ ጣይብ ኤርዶጋን የቱርክን ወታደራዊ አቅም ለፈተና አያቀርቡም፤ ምክንያቱም ጦር ሠራዊቱ ባዶ ቅርፊት ሲሆን የባሕር ኃይሉ ደግሞ ከዚህ የባሰ ሁኔታ ላይ ይገኛል

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና የመካከለኛው ምሥራቅ መሪዎች፣ ሁቲዎች ሞካን በመያዛቸው ላይ ምላሽ ለመስጠት እየተጣደፉ ናቸው፤ ሞካ በባብ ኤል-መንደብ ላይ የምትገኝ ትንሽ ወደብና ከተማ ሲሆን፣ ወደ ቀይ ባሕር መዳረሻን የሚቆጣጠር ስትራቴጂያዊ ጠባብ መተላለፊያ ነው።
ግብፅ በጨዋታው ውስጥ ናት። ግብፅን እንዳትሰምጥ ለማቆየት በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮች ካፈሰሱ በኋላ፣ የሳዑዲ ዘውድ አልጋ ወራሽ ልዑል መሐመድ ቢን ሰልማን ለኢንቨስትመንታቸው ተመላሽ ለማግኘት ይፈልጋሉ። ይህም በቀይ ባሕር ላይ ዋነኛው የወጪ ንግድ ተርሚናል በሆነችው በያንቡ አቅራቢያ የግብፅ ወታደራዊ ሰፈር መቋቋም ሊሆን ይችላል። ካይሮ ከሪያድ ልግስና ባሻገር የምትመለከተው ብዙ ነገር አለ።
ባለፈው ወር ብቻ ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ ከፓኪስታንና ከቱርክ ጋር የተጠናቀቀው የቢን ሰልማን የጋራ መከላከያ ስምምነት የሆነው የመካ ቃል ኪዳን (Mecca Pact) እንዲሁም በአጀንዳው ላይ ይገኛል። ቢን ሰልማን አሜሪካን ለማሳፈርና የ80 ዓመቱ የአሜሪካ-ሳዑዲ የመከላከያ ጥላ የበላይነት ማብቃቱን ለማመልከት ቢሞክሩም፣ ፓኪስታንና ቱርክ ለሳዑዲ ዓረቢያ መከላከያ ይደርሳሉ ወይ የሚለው እስካሁን ግልጽ አይደለም።
በሰሜናዊ ሳዑዲ ዓረቢያ የቱርክ ሰፈር ሊቋቋም ስለሚችል የተወሰነ ውይይት ቢካሄድም፣ ይህ ሳዑዲ ዓረቢያን በሁቲዎች ላይ አይረዳትም። ቢን ሰልማን፣ የቱርክ ፕሬዚዳንት ረጀብ ጣይብ ኤርዶጋን (Recep Tayyip Erdoğan) መካንና መዲናን ዓለም አቀፋዊ ለማድረግና ቱርክ እስራኤልን የምትከብብበትን አቅም ለማጠናከር ካላቸው ፍላጎት ውጭ ስለ ሳዑዲ ዓረቢያ ብዙም እንደማይጨነቁ ያውቃሉ።
ሳዑዲ ዓረቢያ በሁቲዎች ቀጥተኛ ኢላማ ውስጥ ብትሆንም፣ ቀውሱ የቱርክን ወታደራዊ ኃይል አፈ ታሪክ መሆኑንም ያጋልጣል። በወረቀት ላይ ቱርክ ጠንካራ ናት። የኔቶ መሪዎች በወረቀት ላይ በኔቶ ውስጥ ሁለተኛው ትልቁ ጦር ስላላት፣ ቱርክን ቆጵሮስን በመያዟና በኤጂያን ባሕርና በምሥራቅ ሜዲትራንያን በግሪክ ላይ በምትፈጽመው ቅስቀሳ ተጠያቂ ከማድረግ ይቆጠባሉ።
ኤርዶጋን ከምድር ጦራቸው ባሻገር፣ በጥቁር ባሕር፣ በሜዲትራንያንና በኤጂያን ባሕሮች የቱርክን የባሕር ኃይል በሰፊው ከማስፋፋት ጋር ተያይዞ የሚታይ የግዛት ማስፋፋት የባሕር ላይ ፖሊሲ የሆነውን “ሰማያዊ አገር” (Blue Homeland) ለረጅም ጊዜ ሲያስተዋውቁ ቆይተዋል። ቱርክ ሰፈሮችን በመገንባትና በአንዳንድ ሁኔታዎች በተያዘችው ቆጵሮስ፣ በሶሪያ፣ በኳታርና በሶማሊያ አውሮፕላኖችን በማስፈር ሰፊውን ወታደራዊ አሻራዋን አስፋፍታለች። የቱርክ ድሮን መንጋ አስፈሪ ነው።
ቢን ሰልማን የአሜሪካን ድጋፍ መፈለጋቸው እንደተነገረ ሲሆን፣ የF-35 ጆይንት ስትራይክ ፋይተር ሽያጭ ማስታወቂያ አስፈላጊ ቢሆንም፣ ኮንግረስ ባያግደው እንኳ ሥልጠናውና አቅርቦቱ ዓመታትን ስለሚወስድ በሁቲዎች ላይ ምንም ፋይዳ የለውም።
የቱርክ ትልቁ የውጭ ወታደራዊ ሥምሪት አሁን በሶማሊያ ይገኛል። ቱርክ በአገሪቱ የጠፈር ጣቢያ እየገነባች ሲሆን፣ ትልቅ የባሕር ኃይል ሰፈር ትይዛለች፣ እንዲሁም የሞቃዲሾን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ትቆጣጠራለች። ባለፈው አሥር ዓመት ቱርክ በሶማሊያ በሺዎች የሚቆጠሩ የልዩ ኃይል አባላትን አሠልጥናለች።
ታዲያ ኤርዶጋን ባብ ኤል-መንደብ ክፍት ሆኖ እንዲቆይ ለመርዳት የቱርክን የባሕር ኃይል፣ ድሮኖችና ልዩ ኃይሎች በመጠቀም ለቢን ሰልማን መከላከያ ለምን አይደርሱም? በ16ኛውና በ19ኛው ክፍለ ዘመናት በአብዛኛው የኦቶማን ግዛት አሁን በከበባ ውስጥ የምትገኘውን የየመን የቲሃማ ጠረፍ ያስተዳድር ነበር። ኤርዶጋን የቱርክን በሶማሊያ መገኘት ለማስረዳት የኦቶማንን ቀዳሚ ተሞክሮ ቢጠቅሱም፣ ታሪኩን ተሳስተዋል፤ ኦቶማኖች ሶማሊያ ተብላ ወደምትጠራው ግዛት ደርሰው አያውቁም፤ ይልቁንም ቅኝ የገዙት የሶማሊላንድን ሰሜን ምዕራባዊ የአውዳል ክልል ነበር።
ኤርዶጋን ትርጉም ያለው ድጋፍ የማያደርጉበት ምክንያት፣ የቱርክ ኃይል በወታደራዊ ብቃቷ ዙሪያ ባለው እርግጠኛ አለመሆን ላይ የተመሠረተ መሆኑ ሊሆን ይችላል። አዎን፣ ቱርክ ትጥቅ የሌላቸውን ኩርዳውያን ገበሬዎች ስትደበድብ ልዕለ ኃያል ነኝ ልትል ትችላለች፤ ነገር ግን የቱርክ ጦር በእርግጥ ኃያል ቢሆን ኖሮ ከኩርዶች ጋር ባደረገው ከ40 ዓመታት በላይ በዘለቀ አመፅ ላይ ከመቆራረጥ ውጪ ሌላ ውጤት ያስመዘግብ ነበር።
የፖለቲካ ማጽዳቶች—ከአምስት የሠለጠኑ የF-16 አብራሪዎች አንዱ በእስር ላይ ሲሆን፣ አብዛኞቹ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ደግሞ ተተክተዋል—የቱርክ ጦር ባዶ ቅርፊት መሆኑን ያመለክታሉ። የኤርዶጋን ጄኔራሎች እንደ ጣዎስ ሊንቀባረሩ ይችላሉ፤ ነገር ግን የመዋጋት አቅማቸውን እንደያዙ የሚያሳይ ምንም ምልክት የለም። የቱርክ የባሕር ኃይል ደግሞ ከዚህ የባሰ ሁኔታ ላይ ነው። ትጥቅ የሌላቸውን የሴይስሚክ ነዳጅ ፍለጋ መርከቦችን ማስቸገር ይችላል፤ መዋጋት ግን አይችልም። የቱርክ ኃይል የሚመነጨው የጦሩን ባዶነት ከማጋለጥ መቆጠብ ከመቻሏ ነው።
ኧርዊን ሽሮዲንገር (Erwin Schrödinger) በሳጥን ውስጥ ያለች ድመት አንድ ታዛቢ ሁኔታዋን እስኪያረጋግጥ ድረስ ሕያውም ሙትም እንዳልሆነች የሚቆይበትን የ“ሽሮዲንገር ድመት” ታዋቂ የሐሳብ ሙከራ እንዳቀና ሁሉ፣ ዛሬ ኤርዶጋን የ“ሽሮዲንገር ቱርክ” ራስ ላይ ተቀምጠው ነው የሚመሩት። የወታደራዊ ብቃቷ ይገባኛል ጥያቄ የተመሠረተው ያን ብቃት ለፈተና ባለማቅረብ ላይ ነው። ኤርዶጋን የቱርክን ኃይሎች ወደ ባብ ኤል-መንደብ የማያሰማሩት፣ ውድቀትንና ጉራቸው ከባዶ ንግግር ብዙም የማይሻል መሆኑን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዳይረዳ ስለሚሰጉ ነው።